Friday, 24 September 2021 17:07

ከምንጩ እንጠጋ

Written by

የሰው ልጅ በዚህ ምድር ሲኖር ማድረግ ከማያቆማቸው ነገሮች አንዱ እርካታን መፈለግ ነው። መቼም መጠን እና አይነቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው የልቡን ሀሳብ ወይም ክፍተቱን ለመሙላት የቻለውን ርቀት ይጓዛል። የሚገርመው ግን ይህ የልብን መሻት ለመሙላት የሚደረግ ጥረት ማብቂያ የለሽ መሆኑ ነው። በእርግጥ ከትላንትናችን ዛሬ የተሻለ  እንዲሆን ከዛሬያችን ደግሞ ነገ የደመቀ እንዲሆን መመኘት እና መስራት ተገቢ እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ባህሪ ነው። 

ነገር ግን አንዳንዴ ይህን እርካታ ፈላጊ ማንነቴን እርካታን ሊሰጠኝ ከማይችለው መንደር አስጠግቶ ደጅ ሲያስጠናኝ አገኘዋለሁ። ያን ጊዜ ሊያረካኝ በነፃ ከተሰጠኝ ምንጭ ርቄ ብዙ ትንንሽ ጉድጓዶችን ለ ጥሜ ውሀ ፍለጋ እየቆፈርኩ እንደሆነ እረዳለሁ። ይሄን ህይወት ጥቂት የማይባል ክርስቲያን የሚጋራኝ ይመስለኛል። የህይወትን ምሉዕነት ከነገሮች መሳካት እና አለመሳካት ጋር እያዛመዱ መኖር፣ እዚህ ጋር ስደርስ ይህን ሳደርግ እንትን ሲኖረኝ ሁሉ ይሰምርልኛል ያኔ እረካለው ብሎ መልፋት፣ ከህያዉ ውሃ ምንጭ ርቆ የማያዘልቁ የራስ ጉድጓዶችን ሲቆፍሩ መክረም ማብቂያ የሌለው ምኞት ውስጥ ከቶናል። የእምነታችን ጀማሪ እና ፈፃሚ የሆነው ኢየሱስ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም” (ዮሐንስ 6፥35) ብሎ ቃል የገባልን አማኞች ኢየሱስን ከማያውቁት እኩል ያልረካ ማንነታችንን ለማርካት እንቅበዘበዛለን። በእርግጥ እንደ ቃሉ ብንመላለስ ከመርካት የሚጀምር ህይወት እንጂ ለመርካት የሚጀመር ህይወት እንድንኖር ዋጋ አልተከፈለልንም። በዚህም ምክንያት ምድር ላይልብን ጥሎ በዚህ እረካለሁ ማለት እግዚአብሔርንም ማሳዘን ህይወታችንንም ማዛል ይሆንብናል። 

... በእርግጥ እንደ ቃሉ ብንመላለስ
ከመርካት የሚጀምር ህይወት እንጂ
ለመርካት የሚጀመር ህይወት
እንድንኖር ዋጋ አልተከፈለልንም።

 

ለትምህርት እንዲሆነን እግዚአብሔር ህዝቡን የገሰፀበትን ቃል ማየት እንችላለን “ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም ጕድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል” (ኤርምያስ 2፥13)። በእግዚአብሔር ማንነት እና በክርስቶስ በተፈፀመው ስራ ያልረካ ማንነት ሁለት ስህተቶችን ያደርጋል። ትክክለኛውን ምንጭ መተው እና ውሃ ሊይዙ የማይችሉ ጉድጓዶችን መቆፈር። ለዚህም ነው ትጋታችን፣ የልብ ፍላጎታችን፣ ፀሎታችን ለምን እንደሆነ መጠየቅ ያለብን። እንደ ነፍሳችን ያለ ጥልቅ እና ሰፊ ነገር በፈጠረው አምላክ እንጂ በግኡዝ፣ በፍጥረት አሊያም በረቀቀ የሰው ልጅ ጥበብ አይሞላም! ከጥረታችን ለአፍታ አረፍ ብለን ከጀርባ ያለውን ምክንያት እንፈትሽ። ሞልቶ የፈሰሰ ውሀ፣ አጥግቦ የተረፈ መብል ገፍቶ ውሃ እና መብል ፍለጋ ከቤት ርቆ መሄድ እንዳይሆንብን! ከእውነተኛው ምንጭ እንጠጋ! ሌሎቹ ኩሬዎች ናቸው ውሃ የያዙ ቢመስሉም ጠንከር ያለ ፀሀይ በመጣ ጊዜ ይደርቃሉና።  

እግዚአብሔር በራሱ መርካትን ያስተምረን!

 

Tsinat Wondwossen

Tsinat Wondwossen is a young writer passionate about exploring the purpose of life. She enjoys insightful conversations and reflecting on current issues.

white-200.png

Serving Ethiopian women by encouraging and exemplifying vulnerable, thought-provoking conversations around the Gospel of Jesus Christ, the mission of the
Church, and the life of a Christian.

Address
:
Golagul Tower
Addis Ababa, Ethiopia

Emailinfo@selahethiopia.org
selahforethiopia@gmail.com

Follow Us

Subscribe to emails from Selah

We have officially launched our website and all our social media platforms. Please join us, follow, and share. Subscribe to our newsletter bringing you regular updates, resources, and everything in between!

Copyright © 2024 Selah Ministries.
Address: Addis Ababa, Ethiopia 
Emailinfo@selahethiopia.org