Friday, 16 June 2023 13:16

ተመዘኚ!

Written by

እንደወትሮው የሥራ ሰዓት መውጫ ሲደርስ ከምሠራበት ቦታ ወደ ቤቴ ለመግባት በመንገዴ ላይ የባጥ የቆጡን ሳውጠነጥን ጭንቅላቴ በሀሳብ እግሬ በእርምጃ ይሄዳል። በአጋጣሚ የአንድ የልጅ የሚመስል ድምጽ ከጆሮዬ ገባ። "እናት ተመዘኚ" በአስራዎቹ እድሜ መጀመሪያ ያለ የሚመስል ልጅ የሰዎችን ክብደት የሚመዝንበትን መሣሪያ ከእግሩ ስር አስቀምጦ በድካም ስሜት ቆሟል። በእርግጥ ይህ ልጅ የሚመዘንለት አጥቶ የቀን ገቢውን ቢያስብ ነበር "ተመዘኚ" ያለኝ ለኔ ግን መልዕክቱ ሌላ ሆነልኝ። ባለማስተዋል ከምጓዘው የሕይወት መንገድ ያስቆመኝ የአስተውሎት ግብዣ ነበር። በቅጽበት ያለሁበትን ጊዜ እና ልምድ ማሰብ ጀመርኩ። ጊዜው የመመገብ (የመብላት) እንጂ የመመዘን አይደለም። ራሱን እና ሀሳቡን ለሚዛን የሚያቀርበው ጥቂቱ ይመስላል ለዛም ነው ቅርጽ  አልባ ማንነት የበዛው። ይህ ሰውነቴ እንደሚመገበው እና የተመገበውን በለውጥ እንደሚያሳየው አእምሮዬም ከመመገብ አልቦዘነም። ፀሀይ ወጥታ እስክትጠልቅ ከሚታየው፣ ከሚሰማው፣ ከሚዳሰሰው እና ከሚቀመሰው ሁሉ ጋር ስውል ወደ ስጋዬ  ከሚገባው መብል ባለፈ የሀሳብ ማዕበል ወደ አእምሮዬ ይጎርፋል። ታዲያ ፈቅጄለትም ሆነ በሚገባ ሳላጤነው ገብቶ ቤቱን የቀለሰው ሀሳብ ውሎ ያድርና ግብር በመሆን ይገለጣል። ያን ጊዜ ያፈራው ፍሬ ጣፋጭ ይሁን መራር አይቀየርም ውጤት ነውና። በእለት ተእለት ውሎዬ የማስባቸው ሀሳቦች ምን ያህል የሕይወት እርምጃዎቼ ላይ ተፅዕኖ እንዳላቸው ሳስብ ገረመኝ። ምርጫ እና ውሳኔ፣ ከሰዎች ጋር ያለ ግንኙነት፣ ማኅበራዊ ሕይወት እና ሥራ እንዲሁም ሌሎች የሕይወት ክፍሎች በምናስበው ሀሳብ ተፅዕኖ ስር ናቸው። ታዲያ የሀሳቦቼ ግብአቶች ምን ይሆኑ?  ሀሳቦቼን ከየት ይሆን የቀዳኋቸው? ይህን ማወቅ ብዙ አያዳግትም ምክንያቱም ያለሁበት ዘመን ሀሳብ እና መረጃ ያለ ገደብ የሚንሸራሸርበት ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ነውር እና ቆሻሻ አደባባይ ይውላለል፣ ሐጢያት እና ስንፍና በቀልድ ካባ ተሸልመው ይቀርባሉ፣ ረብ የለሽ ነገር የብዙሃንን ትኩረት ይገዛል። እንዲህ በሆነ ዓለም ስኖር የሀሳቤን ልከኛነት የምመዝንበት እና ጤናማ ህይወት የምመራበት መንገድ ይኖር ይሆን?

ያለሁበት ዘመን ሀሳብ እና መረጃ ያለ ገደብ የሚንሸራሸርበት ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ነውር እና ቆሻሻ አደባባይ ይውላለል፣ሐጢያት እና ስንፍና በቀልድ ካባ ተሸልመው ይቀርባሉ፣ረብ የለሽ ነገር የብዙሃንን ትኩረት ይገዛል። እንዲህ በሆነ አለም ስኖር የሀሳቤን ልከኛነት የምመዝንበት እና ጤናማ ህይወት የምመራበት መንገድ ይኖር ይሆን?


መመዘን መልካም ነው! ራስን ለሚዛን መስጠት ስለማንነታችን የሚያሳውቀን ብዙ ነው። ምን ያህል ጤናማ መሆናችንን ይጠቁመናል ደግሞም የትኛውን መቀነስ የትኛውን ማብዛት እንዳለብን ያሳስበናል። ሀሳባችንን ካልመዘንን ግን በስጋ ፈቃዳችን ላይ የተመሠረተ የሕይወት ልምምድ ይኖረናል። ከዚህ አንፃር ለራሴ እየሰጋው ስለሆነ ከማኀበራዊ ሚዲያው፣ ከመጽሐፉ፣ ከፊልሙ፣ ከጓደኞቼ እና በአጠቃላይ ከውሎዬ ፈቅጄም ሆነ ባለማስተዋል ካግበሰበስኳቸው ሀሳቦች ጎጂው አልያም ጥቅም አልባው ውስጤ ዘልቆ ማንነቴን ከሚያንጸው እና ውሎ አድሮ ቅርጽም ጤናም ከሚያሳጣኝ መመዘኑ እንደሚበጀኝ አሰብኩ። የቀለለውን በሚያቀለው የከበደውን በሚያከብደው በልከኛው የእግዚአብሔር ቃል! እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ጸጋ አማካኝነት ወደ እርሱ ቀርበን እንድናወራው ከፈቀደልን ዛሬም በፊቱ በመሆን እና ቃሉን በማስተዋል በመመርመር  ሚዛናችን ልናደርገው ይገባል። የእግዚአብሔር ጸጋ ይርዳን!

 

መዝሙር 139

²³ አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤

²⁴ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።

 

Tsinat Wondwossen

Tsinat Wondwossen is a young writer passionate about exploring the purpose of life. She enjoys insightful conversations and reflecting on current issues.

More in this category: « ከምንጩ እንጠጋ
white-200.png

Serving Ethiopian women by encouraging and exemplifying vulnerable, thought-provoking conversations around the Gospel of Jesus Christ, the mission of the
Church, and the life of a Christian.

Address
:
Golagul Tower
Addis Ababa, Ethiopia

Emailinfo@selahethiopia.org
selahforethiopia@gmail.com

Follow Us

Subscribe to emails from Selah

We have officially launched our website and all our social media platforms. Please join us, follow, and share. Subscribe to our newsletter bringing you regular updates, resources, and everything in between!

Copyright © 2024 Selah Ministries.
Address: Addis Ababa, Ethiopia 
Emailinfo@selahethiopia.org