9ኛ ክፍል እያለሁ አንድ ቀን አባቴ ከትምህርት ቤት መልስ እያደረሰኝ ሁሌ እንደምናደርገው ልብ ለልብ እየተጫወትን ነበር። (እየቀለድኩ ነው) ወላጆቼ 6 ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ቤታችንም ሆነ ከቤት ወጪ ሲያደርሱንና ሲመልሱን ጸጥታና ተረጋግቶ መነጋገር የሚያጋጥመን በጣም አልፎ አልፎ ነው። ሁላችንም ብዙ ጉዳዮችን በአንድ ጊዜ ስለምናወራ አሁን እንኳ አንድላይ ስንሰበሰብ ላልለመደው ሰው ከፍተኛ ትንግርት የሆነ ትርምስ ነው። በዚያን ቀን ግን እህቶቼና ወንድሜ በምን አጋጣሚ እንደሆነ ባላውቅም አብረውን ስላልነበሩ ከፓፕስ (አባቴ) ጋር ለማውራት ቻልን። በቀኔ ውስጥ ስላጋጠመኝ አንድ መልካም ነገር ነገርኩትና “ለነገሩ ማክሰኞ የዕድል ቀኔ (my lucky day) ነው” ብዬ ቀጠልኩ። የተወለድኩበትና ከዚህ በፊትም የምቆጥራቸው ብዙ መልካም ነገሮች ማክሰኞ ቀን እንዳጋጠሙኝ በከፍተኛ ደስታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቼ ልክ እንደጨረስኩ አባቴ መለስ ብሎ “ይህ ጣዖት አምልኮ ነው” ሲለኝ የተሰማኝን ድንጋጤ እስከዛሬ አስታውሰዋለሁ። አባቴ ቀጥሎም በሕይወታችን ለሚመጡ ማንኛውም መልካም ነገሮች እንደምክንያት የምናቀርበው ክስተቱ የተፈጠረበት ቀን፣ የለበስነው ልብስ (“lucky color”)፣ ከምንወደው ሰው ጋር በመሆናችን ወዘተ... ከሆነ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ለሌላ እየሰጠን እንደሆነ ነገረኝ። ሁሌ ከማስታውሳቸው ትምህርቶች አንዱ ነው።
በምን መልኩ ይሆን ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ለሌሎች ወይም ለራሳችን ስንሰጥ የምንገኘው? በተደጋጋሚ ፈተና የሚሆንብኝ ነገር በተለይ ክርስቲያን ካልሆኑ ወይም የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ከማይቀበሉ ሰዎች ጋር በሚኖር ውይይት ነው። አንድ መልካም ነገር በሕይወቴ ለምን እንደሆነ ሳስብ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበልኩት ነገር መሆኑን ምንም ጥርጥር የለኝም፤ ግን ይህንኑ ጉዳይ በእግዚአብሔር ላይ ተመሳሳይ እምነት ለሌላቸው ሰዎች ሳካፍል “ይህንን ያደረገልኝ እግዚአብሔር ነው” ብዬ በግልጽ ከመመስከር ይልቅ እንደዕድል፣ ወይም በእኔ ጥረት እንደተገኘ ነገር አድበስብሼው ሳልፍ ራሴን አገኘዋለሁ። ምንም እንኳን የእኛ ማኅበረሰብ ኃይማኖተኛ ቢሆንም ግን ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ካለው ዓለማዊነት (secularism) የተነሳ ተመሳሳይ እምነት ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ስንነጋገር የእግዚአብሔርን ስም ለመጥራት፣ ስላደረገልን ነገር በግልጽ ለመናገር እናመነታለን። በሕይወታችን ያለ ማንኛውም መልካም ነገር የመጣው በሌላ ምክንያት ወይም በራሳችን ጥረትና ጉብዝና እንደሆነ ካሰብን ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ለሌላ እየሰጠን ነው። አንዳንዴ ደግሞ የውሸት ትኅትናን በመምረጥ መልካም ነገሮቻችንን ሰዎች ሲያነሱ “አይ እሱ እኮ ምንም አይደለም” ብለን እናልፈዋለን - ይህን በማድረግ የእግዚአብሔርን ታላቅ ተዓምርና በጎነቱን እናሳንሳለን።
በዚህ ምድር ላይ ያለን ዋና ተልዕኮ ለሌሎች የእግዚአብሔርን መልካምነት መመስከር፣ ታላቅነትና ጽድቁን ማሳየት ነው። በሕይወታችን የሚታዩት ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸው መልካም ነገሮች ለዚህ ተልዕኮ መንገድ የሚከፍቱ ዕድሎች ናቸው። የእግዚአብሔርን ተዓምራትና የእርሱን በጎነት እየቆጠርን እርሱን ስናመሰግን ልባችን በሌላ ምስጋና ይሞላል፣ የሚትረፈረፍ ደስታና አመስጋኝነት መለያችን ይሆናል። ሰዎች ሕይወታችንን በማየትና (በሥራ፣ በቤተሰብ፣ በሀብት፣ በጓደኞች፣ በባህሪያችን፣ በትምህርታችን ... ሊሆን ይችላል) እግዚአብሔር ያሳካልንን ነገሮች በመቁጠር “ውይ እንዴት ዕድለኛ ነሽ” ሲሉ፣ ዕድል ሳይሆን ከእርሱ የተቀበልነው ተዓምር መሆኑን በመመስከር የመልካም ስጦታ ትክክለኛው ምንጭ የሆነውን እግዚአብሔርን እንዲያዩ መንገድ እንክፈት።
“ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ”
በኢሳይያስ 43፡10