መሄድ ብቻውን የሚያደርስ፣ መቆም ደግሞ ሁል ጊዜ የሚያዘገይ ይመስል ህይወታችን መፍጠን ብቻ ሆኗል። ትላንታችንን ጠልተን ዛሬያችንን ሳናዳምጥ ነገ ሲመጣ ለመኖር ይቀለናል። እግዚአብሔር በህይወታችን እንድንፈጥን ብቻ ሳይሆን ቆም ብለን እንድናስተውል ይፈልጋል፤ ነገር ግን የአብዛኞቻችን ህይወት ከዚህ የራቀ ይመስላል። በህይወቴ የመቆምን ጥቅም ተምሬያለሁ። በፊት ከወደቅኩበት መሬት እንደተነሳሁ ህመሜን ሳልታከም፣ የመታኝን እንቅፋት ሳላስተውል፣ ልብሴ ላይ ያለውን አቧራ ብቻ አራግፌ (መውደቄን እንዳያሳብቅብኝ መሆኑ ነው እንግዲህ) ጉዞዬን ስቀጥል በተመሳሳይ እንቅፋት የመውደቅ እድሌን እንዳሰፋሁ ሳላስተውል ወደፊት መፍጠን ብቻ ወደ ፊት የሚያደርስ ይመስለኝ ነበር።
ዝም ብሎ መሄድ እንዴት ያደክማል መሰላችሁ! ህይወትን ያዝላል፣ መነሻ ላይ የነበረንን አቅም ያሳጣል፣ ማንነትን ይሸራርፋል፣ ስሜትን ያዋዥቃል። የመጡበትን ወደኃላ፣ ያሉበትን በማስተዋል የሚሄዱበትን በትኩረት መመልከት ግን ትልቅ ትርፍ አለው። መድረስ ያለው በመፍጠን ውስጥ ብቻ ሲመስለን በመፍጠን ውስጥ ከብዙ ነገሮች መዘግየትም እንዳለ አናስተውልም። ፈጥኖ እንደመዘግየት ያለ ህመም ደግሞ ከባድ ነው ሲወራም ሲኖርም አያምርም። የዘገየሁት ስለፈጠንኩ ነው ብል አሁን ለማን ይገባል? ምናልባት ለትራፊክ ፖሊስ... ስቀልድ ነው።
ስለመቆም እና ህይወት ላይ ስለማተኮር ሳስብ ቅድም እንደፃፍኩት ሶስት ጊዜያቶችን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፤ እነርሱም ትላንት፣ዛሬ እና ነገ ናቸው። እነዚህን ጊዜያቶች አለማስተዋል ወይም በአግባቡ አለመረዳት ቆም ብለን እንዳናተኩር ያደርገናል። ስለ ትላንት ስናስብ እንደያለፍንበት መንገድ በአእምሯችን የደስታ እና የውጤታማነት አሊያም ደግሞ የድብርት እና የክስረት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ሁለቱንም ተቃራኒ ስሜቶች ግን በ እግዚአብሔር መልካምነት ማለፋችንን ብናስብ፣ ነገን ደግሞ ለእርሱ አደራ ሰጥተን በእርሱ ምሪት እያየን፣ ለዛሬ ደግሞ ተስፋ እና ትምህርት ይሆነናል።
ስለ ዛሬ ደግሞ ስናስብ የፈለግነው ላይ በመድረሳችን ደስተኞች፣ የማንፈልገው ላይ በመቆማችን ሁሌ የምናማርር ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን ዛሬን በፈቃዳችን ወይም በጥረታችን እንዳላገኘነው ብናስብ ዛሬን ከእግዚአብሔር ለተሰጠ አላማ እንደታደልነው እንረዳለን ይሄም ለውጤት ይመራናል።
እንግዲህ የቀረን ነገ ነው፤ ልናስብለት እንጂ ልንጨነቅለት የማይገባው ነገ… በእግዚአብሔር እጅ ያለው ነገ! ስለዚህ እንዲሁ እየፈጠኑ ከመሄድ እንቁም! የመጣንበትን መንገድ ለጉዳታችን ሳይሆን ለጥቅማችን ለማየት እንቁም! የዛሬን ምንነት ለመረዳት እና የተረዳነውን ለመኖር እንቁም! መንገዳችንን ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር አስማምተን መድረስ ወዳለብን ለመድረስ እስኪ እንቁም! የእግዚአብሔር ሀሳብ ይደግፈናል ትኩረትን ያስተምረናል የሚቀጥለውን ጎዳና ያቀናልናል!
“መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።”
— መዝሙር 119፥59 (አዲሱ መ.ት)