መንትያ ልጆችን እግዚያብሄር በአደራ ከሰጠን አመት ከመንፈቅ ሆነን። ከምኑም እንዳንጎል፣ ተባዕት እና እንስት አድርጎ አስረከበን፣ ክብሩ ይስፋ!
ውድ ባለቤቴና እኔም ገፀ በረከቶቻችንን የምናሳድግበትን መንገድ ለመቅረፅ ጥረት እናደርጋለን። ከነዚህም መሃከል ፣ አገርኛ የሆነውን ከመልካም ቤተሰቦቻችንና ማህበረሰባችን የወረስነውን ስነምግባር ለነርሱም ማስተላለፍ ነው።
ምንም እንኳን አንደበታቸው ገና ባይፈታም፣ አይናቸው እና ልቦናቸው ክፍት ነውና ከማስተማር አልታገድንም። ከስነምግባር ትምህርታቸው መሃከል አንደኛው “አንድን ነገር ስትፈልጉ በማልቀስ፣ በመጮህ፣ በመንፈራገጥ ፈንታ መዳፋችሁን ለልመና ዘርጉ። የጠየቃችሁትን ደግሞ ስትቀበሉ፣ አንገታችሁን ሰበር በማድረግ እጅ ነስታችሁ ከምስጋና ጋር ተቀበሉ” አልናቸው። “አይናገሩም፣ ህፃናት ናቸውና አይገባቸውም!” ብላችሁ በጭራሽ እንዳታስቡ! እምብዛም ሳይዘገዩ ተግባራዊ ሆነ።
የሚገርመው ግን እኛ ልናስተምር ተነስተን እነርሱ አስተማሩን። ልጆቹ ምን ማድረግ ጀመሩ መሰላችሁ? የጠየቁንን ሳንሰጣቸው በፊት አጎብድደው ያመሰግኑን ገቡ። በትህትናቸው ተበተቡን። ገዙን።
ታድያ እኔም ቆም ብዬ አስተዋልኩ… ቃሉን አስታወስኩ።
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። (ዕብራውያን 11፥1)
ኢየሱስም፥ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው። (ዮሐንስ 20፥29)
አምላክ ሆይ ልጆቼ እንዳመኑኝ ልመንህ፣ እንዳመሰገኑኝ ላመስግንህ፣ ልስጣቸው አልስጣቸው፣ ይቀበሉ አይቀበሉ ሳያውቁ እንዲሁ አመሰገኑ። እኔንም እንዲሁ ለምስጋና ቅርብ የሆነ ልብ ስጠኝ።