አቤት በአንቺ ላይ ያለው የቃሉ መገለጥ!
አቤት የተሰጠው ህይወትሽ!
አቤት በእግዜር ህዝብ መሃል ይዘሽው ምትገቢው ድባብ!
አቤት ቃላቶችሽ!
አቤት ምክር አሰጣጥሽ!
አቤት አስተምህሮሽ!
አቤት! አቤት! አቤት!
ተው! ተው አትካቡኝ፣
ትዕቢት እንዳይንደኝ
ተው! ተው አታግዝፉኝ፣
እኔነት እንዳያንቀኝ
እኔ እኮ ቧንቧ ነኝ፣
በበላይ ትዕዛዝ የተተከልኩኝ
እኔ እኮ ባሪያ ነኝ፣
ተጠሪ አዛዥ ያለኝ
እኔ እኮ አውራጅ ነኝ፣
ያለ ውሃው ምንጭ ዋጋ የሌለኝ
ተው! አትካቡኝ፣
ትምክህት እንዳይነቅለኝ
ብናገር፣ ሞገሴ
ባስተምር፣ ጥበቤ
ቢወራልኝ፣ ክብሬ
ብመክር፣ ተመክሬ
ብምር፣ ተምሬ
ብወድድ፣ ተፈቅሬ
ብታይ፣ መድመቂያዬ
ብመካ፣ በጌታዬ
ቧንቧ ብሆን፣ በርሱ ተተክዬ
ባፈስ፣ ከምንጩ መንጭቼ
አንድን ነገር ልብ አልኩ በዘመኔ የውሃን ቧንቧ ሲያመሰግን ያየሁት የለም እኔ
ዋናው ውሃው ነው!
ዋናው ከእርሱ ነው!
ዋናው በእርሱ ነው!
ዋናው ለእርሱ ነው!
ዋናዬ 'ዋና' ነው!
ይልቅስ......
ባልተጨበጠ ደስታ እንዳልታበይ፣
አውቃለሁ ብዬም ማወቅ እንዳላቆም፣
ከእርሱ ዝቅ ብዬ እንድማር እንደ ማሪያም፣
እንዳልቅበዘበዝ እንደ ማርታ፣ እንድጀግን እንደ ጢሞቲዮስ፣
ትሁት እንድሆን እንደ ክርስቶስ፣
እንዳውቅ እንደ ጳውሎስ፣
ልቤን እንዲከፍተው እንደ ሊዲያ፣
ያለ ግዜዬ እንዳልታይ እንዳልታበይ
ፀልዩኝ ማልዱልኝ!
መታሰቢያነቱና የፀሎት ሸክሙ ለሁላችን፣ በተለይም ለሚያገለግሉን የእግዜር ባሪያዎች ይሁንልኝ።
ቤ.ካ
2012 ተፃፈ