ስለኢየሱስ ልደት ስናነብ በክስተቱ ዙሪያ የነበረውን ታላቅነትና ግርማዊነት ላናስተውል አንችልም፦ መልዓኩ ገብርዔል ለማርያምና ለዮሴፍ ሲገለጥ፤ መላዕክት ለእረኞች ሲገለጡ የነበረው ታላቅ ብርሃንና የመላዕክት ዝማሬ፤ ጠቢባኑን የመራው ኮከብና እነሱ ያመጧቸው ስጦታዎች፤ ስምዖን ስለሕጻኑ የተናገረው... በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ስለኢየሱስ ልደትና ስለምሥራቹ ሳስብ በጣም የሚደንቀኝ ይህ ታላቅ ዜና በከተማው የተሰራጨው ከሜዳ በመጡ እረኞች መሆኑ ነው። (ሉቃስ 2፡17)
ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤ እላችኋለሁና፣ ብዙ ነብያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም” አላቸው። (ሉቃስ 10፡23) ደቀመዛሙርቱና ተከታዮቹ ተራ ሰዎች ነበሩ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ታላቅ ዜና ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውሮ ለሕጻናት ለመግለጥ ወደደ። (ሉቃስ 10፡21)
ወንጌሉ በዓለም ሁሉ ዙሪያ የተሰራጨው በእነዚህ እንደሕጻናት በነበሩ፣ ሰው ከሆነው አምላክ ከኢየሱስ ጋር ተራምደው እውነቱን ባዩና በሰሙ ተራ ሰዎች ነው።
ዘማሪዋ እንዳለችው፦
“ተነገረ ምስራቹ ሜዳ ባደሩ እረኞች
ወንጌሉ ተሰበከ ባልተማሩ አሣ አጥማጆች
ጥበበኞችን ሊያሳፍር የዓለም ደካሞችን መረጠ
የከበሩትን ሊያሳፍር ምናምንቴውን አከበረ”
ይህ ባይሆን ኖሮ ዛሬ የት እንሆን ነበር ይሄኔ?
መንፈስ ቅዱስ ለነፍሳችን ሕይወት እየሰጠ በጸጋ ወዳለው መዳን ይመራናል፤ ይህ ቸር መንፈስ በኢየሱስ የተሰጠንን ይህንን ተስፋ ያረጋግጥልናል፣ በድካማችን እየደገፈ ከባድና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን እንድናልፍ ያደርገናል።
“ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደእናንተ እመጣለሁ።” (ዮሐ. 14፡18)
ጸሎት
ሊያድነን ለመጣው እግዚአብሔር ክብር ይሁን! እውነቱን ለገለጠልን አምላክ ክብር ይሁን! በእውነቱ ለሚያጸናን ጌታ ክብር ይሁን!