Tuesday, 04 January 2022 09:44

ቀን 12:- የማርያም ምሳሌ

Written by

የኢየሱስን ልደት ታሪክ ሳነብ የማርያም ሚና እንደአዲስ አስገረመኝ። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ደግመን ደጋግመን ያነበብነው ቢሆን እንኳ እንደገና አዲስ ነገር እንማርበታለን ፟- አስደናቂ ነው። ቃሉ እውነትም ሕያው ነው!

የማርያም ታሪክ ሲጀምር በጣም የከበረ ነው። መልዓኩ ሲጎበኛት ሕይወቷ ተቀየረ፤ ቃል ተቀበለች - የዓለም መድኃኒት የሆነው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትወልድ። ባትረዳውም እንኳን ቃሉን ተቀብላ ሕይወቷን ለእግዚአብሔር ሰጠች። ይህንን ዜና ከሰማች በኋላ የሚመጣውን ነገር እያሰበች በጣም የተደሰተች ይመስለኛል። ትንሽ ወጣት የነበረችው ማርያም በዚህ ደረጃ ዓለምን ለማዳን እግዚአብሔር ሊጠቀማት መሆኑ፣ የእግዚአብሔር መልዓክ ሊያናግራት መምጣቱ... ይህ ሁሉ እንዴት አስደናቂ ነው! በጣም ልዩ እንደሆነች እንደተሰማት አስባለሁ። ወዲያው ኤልሳቤጥን ልትጎበኝ ሄዳ ደስታዋንም አካፍላታለች። (ሉቃስ 1፡ 46-55) 

ይህ ደስታዋ ግን ለረጅም ጊዜ አልቆየም። ያላገባች ነፍሰ ጡር ሴት ስትሆን የሚደርሷት ብዙ ግልምጫዎች ደስታዋን እንዳጨለመባት እገምታለሁ። ከዚያም ደግሞ በከብቶች በረት ልጅ መውለድ፣ ትንሹን ልጇን በግርግም ውስጥ ማስተኛት? ምንም የከበረ ወይም ማራኪ ነገር የለውም። ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ብዙ ጠላቶች ሲኖሩት፣ ስለሱ ሰዎች የሚሉትን፣ ስለሷም የሚሉትን ስትሰማ የሚከብድ እንደሚሆን መገመት እንችላለን። በመጨረሻም ልጇ እንደወንጀለኛ በመስቀል ላይ ተሰቃይቶ ሲሞት ስታይ - ከዚህ የሚብስ ምን አለ? ማርያምን መሆን አያስመኝም። 

ከእግዚአብሔር ቃል ስንቀበል በእግዚአብሔር በመመረጣችን የሚሰማውን ክብር ብዙዎቻችን ልናውቀው እንችላለን። “አሜን” እያልን በደስታና በሐሴት እንቀበለዋለን። ነገር ግን የተስፋ ቃሉ እስኪፈጸም ጉዞው ባልጠበቅነው ተራራዎችና ሸለቆዎች መካከል ይወስደናል። በዚህ ሁሉ እንዴት ልንጸና እንችላለን? 

በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ስለማርያምና እምነቷን እንዴት ትገነባው እንደነበር ትልቅ ነገር እንማራለን፦ 

“ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።” ሉቃስ 2፡19

“እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።” ሉቃስ 2፡51

ማርያም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በውስጧ ይዛ እንዳቆየችው ሳስተውል ተገረምኩ። ጉዟችንንና ቁልፍ ክስተቶችን ከቅርብ ጓደኞቻችን ጋር መካፈሉ በጣም ጤናማ ቢሆንም በመንገዳችን ልንጸና የምንችለው በልባችን ባስቀመጥነው እውነት ኃይል ነው - በቀንና በሌሊት የምናሰላስለው በልባችን ያስቀመጥነውን ስለሆነ። ማኅበራዊ ገጾቻችን ከሚሉት ይልቅ በሃሳባችን ያስቀመጥነው ነገር ትልቅ ኃይል አለው። 

በዚህ ገና አንድ ነገር እናድርግ? እግዚአብሔር ለእኛ ያላቸውን የተስፋ ቃሎች በልባችን መጠበቅ፤ በቃሉ ያሉትን ማረጋገጫዎች በልባችን ለመመዝገብ፤ የእግዚአብሔርን ታማኝነት እያስታወስን በልባችን ሀብት መሰብሰብ!

 

ጸሎት

እግዚአብሔር ሆይ፣ ስለ ህያው ቃልህ አመሰግንሀለሁ። ጌታ ሆይ፣ በቃልህ እውቀት እና እምነት በርትቼ፣ የህይወትን ውጣ ውረድ በአንተ ላይ ተደግፌ እንዳልፍ፣ እምነቴን እንድጠብቅ አንተ እርዳኝ። በብርቱ እጆችህ ያዘኝ። ለአንተ ያለኝን ፍቅር ጨምርልኝ። አሜን

white-200.png

Serving Ethiopian women by encouraging and exemplifying vulnerable, thought-provoking conversations around the Gospel of Jesus Christ, the mission of the
Church, and the life of a Christian.

Address
:
Golagul Tower
Addis Ababa, Ethiopia

Emailinfo@selahethiopia.org
selahforethiopia@gmail.com

Follow Us

Subscribe to emails from Selah

We have officially launched our website and all our social media platforms. Please join us, follow, and share. Subscribe to our newsletter bringing you regular updates, resources, and everything in between!

Copyright © 2025 Selah Ministries.
Address: Addis Ababa, Ethiopia 
Emailinfo@selahethiopia.org