Living and Thriving with Grace (“በጸጋ መኖርና መትረፍረፍ”) የሚባል የድጋፍ ቡድን አባል ነኝ፤ በወር ሁለት ጊዜ እየተገናኘን እርስ በርስ እንበረታታለን፣ ሕይወታችንን እንከፋፈላለን። አንድ የሚያደርገን ነገር እያንዳንዳችን ሊድን የማይችል፣ ደረጃ 4 ካንሰር እንዳለብን በሕክምና መረጋገጡ ነው። ምክክሮቻችን ጠለቅ ያሉና የከበዱ እንደሆኑ መገመት ትችላላችሁ። ብዙ ጊዜ ያሉብንን ውሱንነቶች እያነሳን እንወያያለን። የካንሰር ሕክምና ኑሮን ሙሉ በሙሉ ቀይሮ፣ ማድረግ የምትችሏቸው ነገሮች ላይ ብዙ ገደቦች ያደርጋል። ግን ካንሰር ብቻ ሳይሆን ሕይወት ባጠቃላይ ብዙ የማትጠብቋቸውን ነገሮች ታመጣለች።
በጣም ከምወዳቸው ሰዎች መካከል ጃኒ ኤሪክሰን ታዳ የተባለችው አስደናቂ ምስክርነት ያላት ሴት ናት። ጃኒ ታዳጊ ወጣት እያለች በዋና ላይ በደረሰባት አደጋ የእጅና የእግር ሽባነት ቢደርስባትም ስለአካል ጉዳተኝነት ብዙ መጻህፍት ጽፋለች፣ ዓለም ዓቀፍ ተናጋሪና ተሟጋች በመሆኗ የታወቀች ናት። በመጽሃፍ ቅዱሳችን እንዲሁ ትልቅ ፈተና የተጋረጠባት ወጣት ሴት እናያለን፦ ትሁቷ ማርያም “ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” አለች (ሉቃስ 1፡46-47) ነገር ግን ከፊቷ ያለው ከባድ ሕይወት ነበር። መልዓክ ተገልጦ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የሌለው የታላቁን ልዑል ልጅ እንደምትወልድ ሲነግራት እንዴት አስደናቂ እንደሆነ አስቡት! ነገር ግን ማርያም ከመጀመሪያው አንስቶ ብዙ ችግሮች ገጥመዋታል፦ ልጇን የምትወልድበት ቦታ አላገኘችም፤የዓለምን መድኃኒት በግርግም ወለደች፤ ትንሽ ሕጻን ይዛ ወደግብጽ ተሰደደች፤ በናዝሬት አሳደገችው፤ ታላቅ ተዓምራትን ሲያደርግ ቆይቶ... ሲከዱትና ሲሰቅሉት አየች። ለእናት የልጅን ስቃይና ሞት ማየት እንዴት ከባድ ነው! ግን ማርያም ተማምና ብዙዎች ብጽዕት እንደሚሏት ተናገረች።
ታዲያ መባረክ ምንድነው? ሙሉ ጤና ሆኖ ያለ ችግርና ተግዳሮት መኖር ነው? ወይስ ከዚያ የሚበልጥ ነገር አለ? የማርያምን ሕይወት ሳይ፣ የጃኒን ሕይወት ሳጠና፣ ወይም በካንሰር ድጋፍ ቡድናችን ውስጥ ያሉትን ጓደኞቼን ስመለከት አጠቃላይ ምልከታዬን የሚቀይረውን ነገር ተረዳሁ፦ መልዓኩ ገብርዔል ለማርያም ሰላምታ ሲሰጥ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ...ጌታ ከአንቺ ጋር ነው!” አላት። በሕይወት ውስጥ ምንም መከራ ቢገጥመን ጌታ ከእኛ ጋር መሆኑን ካወቅን የማናሸንፈው ነገር አይኖርም። ግን ደግሞ እውነቱን ስንነጋገር በከባድ ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ብዙ ጊዜ ላይሰማን ይችላል።
እንዲህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ስሆን ያገዙኝን ነገሮች ላካፍላችሁ፦
- ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት፦ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያሉት ተስፋዎች የሚገለጡልን ከእርሱ ጋር ግንኙነት ሲኖረን ብቻ ነው። ጨለማና ኃጥያት ከእግዚአብሔር ስለለዩን በምድር የተትረፈረፈ እንዲሁም ዘላለማዊ ሕይወት ልናገኝ የምንችለው ከእርሱ ጋር የግል ግንኙነት ስንመሰርት ነው። በዕብራውያን 10፡19 ላይ ወደቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት ያገኘነው በኢየሱስ ደም እንደሆነ ይነግረናል። ኢየሱስ ወደሕይወትሽ እንዲገባ ጠይቀሽዋል?
- የእግዚአብሔር ቃል፦ በፈተና ውስጥ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር እንዳለ የሚያረጋግጥልኝ ቃሉ ነው። መጽሃፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እና በሰዎች ሕይወት እርሱ ያደረገውን ታላቅ ተዓምራት በሚናገሩ ታሪኮች የተሞላ ነው። እነዚህን ተዓምራት ያደረገው የሰማይና ምድር ፈጣሪ ዛሬም በእኔ ሕይወት እየሰራ መሆኑን ማወቅ ትልቅ እረፍትና መጽናናት ይሰጠኛል። በራሴም ሕይወት ያየኋቸው ብዙ ተዓምራቱ ይህንን ያጸናልኛል።
- የአማኞች ሕብረት፦ በአካባቢሽ ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው? እግዚአብሔር በሕብረት እንድንኖር ይፈልጋል፤ ታላቅ ፈተና ሲገጥመን ከወንድሞችና እህቶች የምናገኘው ማበረታታት፣ ፍቅርና ጸሎት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ የምናውቅበት ሌላው መንገድ ነው። ከካንሰር ጋር በመኖር በገጠመኝ ፈተና አብረውኝ እንዲጓዙ እግዚአብሔር በሕይወቴ ስላመጣቸው ሰዎች ሁሌም እደነቃለሁ። ብዙ ጊዜ የጠበቋቸው ሰዎች አይደሉም። ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እንጂ እኔ ስላደረኩላቸው ብድር የሚመልሱ ሰዎች እንዳልሆኑ አይቼበታለሁ። እግዚአብሔር አስደናቂ አባት ነው። ምንም ውለታ ያልዋላችሁላቸው ሰዎች ብዙ ደግነት አሳይተዋችሁ ተደንቃችሁ ታውቃላችሁ? እግዚአብሔር በእነርሱ ተጠቅሞ እየባረካችሁ ነው።
እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር እንደሆነ አውቀሽ ስትኖሪ እንደማርያምና እንደጃኒ በሕይወትሽ የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደሆነ ታስተውያለሽ። በምንም ነገር ውስጥ እያለፍሽ ቢሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአንቺ ያዘጋጀውን መልካም ሥራ ለመሥራት በክርስቶስ የተፈጠርሽ የእግዚአብሔር እጅ ሥራ እንደሆንሽ አስታውሺ (ኤፌሶን 2፡10)። አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኔ ጋር እንደሆነ አውቄ ለመኖር የዘወትር ጸሎቴ ይህ ነው።
ጸሎት
እግዚአብሔር ሆይ፣ ስለዚህ ቀን አመሰንሀለሁ። በአንተ መገኘት እና በአንተ እርዳታ የማልወጣው የህይወት ተግዳሮት እንደሌለ አውቃለሁ፣ በዚህ እውቀት አርፌ በአንተ ያለኝን ደስታ፣ ከአንተ ጋር ያለኝን ቅርበት፣ ስለ ቃልህ ያለኝን የማሳድግበትን ህይወት እንድኖር እርዳኝ። አሜን
ማጠቃለያ
በዚህ የጸሎት ዲቮሽናል አብራችሁን ስለሄዳችሁ እናመሰግናለን። ለገና ያዘጋጀነው የጥሞና ጊዜ ዛሬ ቢያበቃም፣ በሶሻል ሚዲያ ገጾቻችን በየሳምንቱ የሚያንፁ እና የሚያስተምሩ ቪዲዮዎች፣ መጣጥፎች እንዲሁም ምልከታዎች እናጋራለን፣ በዚያ ይከተሉን። እናመሰግናለን። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን።