Wednesday, 29 December 2021 00:00

ቀን 8:- ቃል ሥጋ ሆነ

Written by

“ቃልም ሥጋ ሆነ፣ በመካከላችንም አደረ” ዮሐ. 1፡14

የገና ወቅት በጣም ደስ ይለኛል! የገና መዝሙሮች አዘጋጃለሁ፤ ለቤተሰብና ጓደኞቼ የእንኳን አደረሳችሁ ካርዶች መጻፍ ያስደስተኛል። የኢየሱስን ልደት የሚተርኩትን የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎች ደጋግሜ እያነበብኩ በዚህ አስደናቂ ታሪኩ ውስጥ ያሉትን ገጸ ባህርያት በየተራ ለማስተዋል እሞክራለሁ። 

ዮሐንስ በትረካው “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን” ይለናል። (ዮሐ. 1፡14) ዮሐንስ በዚሁ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ ዘላለማዊና ሁሉን ዐዋቂ እንደሆነ የገለጸው ይሄው ቃል ሥጋ ሆኖ በመካከላችን ማደሩ ሁሌም ያስደንቀኛል። በየጊዜው ስለሚነገርና ስለለመድነው የዚህን ሀሳብ ታላቅነት ሙሉ ለሙሉ የምንረዳው አይመስለኝም። 

ኢየሱስን ሕጻን ልጅ ሆኖ አስባችሁት ታውቃላችሁ? በስዕል ወይም በቅርጻቅርጽ ካየነው ባለፈ በጥልቀት አስበነው እናውቃለን? ይህንን ራሴን እንድጠይቅ ያደረገኝ አንድ ጊዜ የወጣቶች መጋቢያችን የጠየቀን ጥያቄ ነው፦ ኢየሱስ ልጅ ሆኖ ከጓደኞቹ ጋር ኳስ ሲጫወት አንዱ ልጅ ሲጠልፈው አስባችሁ ታውቃላችሁ? ለአእምሯችን የራቀ ሃሳብ ነው። 

እንደአዲስ እናት የ6 ወር ልጄ ነገሮችን ለመያዝ፣ ለመገለባበጥ ሲሞክር፤ እንቅልፉ ሲመጣ ሲነጫነጭ... እያየሁ ኢየሱስ ልክ እንደዚህ ሕጻን ሆኖ በመካከላችን ማደሩን እያሰብኩ እደነቃለሁ። በመጀመሪያ የነበረውና በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቃል እንደአንድ አቅም የሌለው ሕጻን ሆኖ ወደኛ መጣ - እንዴት አስደናቂ ነው! “ትሁት” የሚለው እንኳን አይገልጸውም። ይህ ሞኝነት የሚመስለው ጥበብ ተመሳሳይ የሌለው ነው! (1ቆሮ. 1፡27) 

የእስራኤልን መጽናናት ሲጠብቅ የነበረው ጻድቅና ትጉህ ስምዖን ይህንን ሕጻን ሲያይ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንዲህ አለ፦ 

“ጌታ ሆይ... ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና። 

ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።” (ሉቃስ 1፡30፣ 32)

 

ጸሎት

መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ በዚህ ትሁት ጅማሬ የሰጠኸንን ታላቅ ጸጋ ማየት እንድችል ዓይኖቼን ክፈት! ሥጋ ሆኖ በመካከላችን ባደረው ቃልህ የሰጠኸውን ማዳን እንድረዳ ምራኝ! በጽድቅህ በመደነቅ ጠብቀኝ። ሕይወት ለሚሰጠው መገኘትህ አመሰኝሃለሁ! አሜን!

white-200.png

Serving Ethiopian women by encouraging and exemplifying vulnerable, thought-provoking conversations around the Gospel of Jesus Christ, the mission of the
Church, and the life of a Christian.

Address
:
Golagul Tower
Addis Ababa, Ethiopia

Emailinfo@selahethiopia.org
selahforethiopia@gmail.com

Follow Us

Subscribe to emails from Selah

We have officially launched our website and all our social media platforms. Please join us, follow, and share. Subscribe to our newsletter bringing you regular updates, resources, and everything in between!

Copyright © 2025 Selah Ministries.
Address: Addis Ababa, Ethiopia 
Emailinfo@selahethiopia.org