በየአመቱ በሰንበት ትምህርት ቤታችን የገናን በዓል ለማክበር ስንዘጋጅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የክርስቶስን መምጣት የሚጠቁሙትን አስደናቂ የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃላት እንቃኛለን። ምንባቦቹ በደንብ የሚያወቁም ቢሆኑ መሲሑ “ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ” እንዴት እንደሆነ እንደገና ለማሰላሰል እድል ይሰጣል። ሁልጊዜ ለሀሳቤ የሚከብደኝ የክርስቶስ አንዱ ባሕርይ ግን የዋህነቱ ነው። ኢሳይያስ መሲሑ “አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም። የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም” ሲል ይነግረናል። ኢየሱስ ራሱ “የዋህ፣ በልቡም ትሑት” እንደሆነ ነግሮናል።
ኢየሱስ የእሱን ፈለግ እንድንከተል እየጋበዘን “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።” እያለ ያበረታታናል። የዋህ ሲተረጎም “የተረጋጋ፣ ገር እና እሺ ባይ” ሊባል ይችላል። እግዚአብሔር የዋህ እንድንሆን ሲል ታዲያ ይህን ማለቱ ነው? ይህ ዓለም እንድናደርግ ከሚያስተምረን ነገር ሁሉ ጋር ተቃራኒ በመሆኑ ለመዋጥ በጣም ከባድ ይሆንብናል። አለም “ምንም ዋጋ ቢያስከፍል ወደ ላይ መገስገስ፣ ማንም እንዲረጋገጥብን ወይም ወደ ታች እንዲያየን አለመፍቀድ፣ ሁሉንም ሰዎች ቦታቸውን ማሳየት… “ ትለናለች፣ ‘ጸጥ በማለት፣ ገር እና ታዛዥ’ በመሆን በሕይወት ውስጥ ስኬታማ ለመሆን እንዴት ተስፋ ልናደርግ እንችላለን? ኢፍትሐዊ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ በምንኖርበት ጊዜ አምላክ ከእኛ ይህን የሚጠብቀው እንዴት ነው?
ባለፉት ዓመታት፣ በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ የዋህ እና ዝምተኛ የመሆንን እውነተኛ ትርጉም ለመረዳት እየታገልኩ ነበር። በማህበራዊ ግንኙነቶቻችን፣ በየስራ ቦታችን፣ ሰዎች እኛን እንደሞኝ አድርገው ሲወስዱን እና ሲጠቀሙብን፤ ትዕግስታችንን ሲፈትኑ እና በዝምታችን ተበረታተው ሲገፉበት - እንደ ክርስቲያን ምን ምላሽ መስጠት አለብን? በእርግጠኝነት፣ እግዚአብሔር ዝም እንድል እና እንድተወው ሊጠብቀኝ አይችልም ብለን እናስባለን። ክፉን በክፉ ባልመልስም እንኳ ቢያንስ እንደበደሉኝ እንዲገነዘቡ ጆሮ ዳባ ልስጥላቸው እንላለን። ለበቀል ስንዘጋጅ፣ ለራሳችን “ይህ ስለ ፍትህ፣ ስለ ለእውነት መቆም ነው” ብለን እናባብለዋለን። በዝምታ መታገሳችን ማንንም የሚጠቅም አይመስለንም።
እኛ ግን ለራሳችን ታማኝ መሆን እና መጠየቅ አለብን፣ እውነት ስለ ፍትህ ነው ወይስ ስለ ተጎዳው ኩራቴ ነው? ብዙ ጊዜ መቀበል ከምፈልገው በላይ፣ የክርስቶስን የየዋህነት ምሳሌ ለመከተል የሚገድበኝ ኩራቴ እንደሆነ ተረድቻለሁ። ኢየሱስ ዛሬ እየጠራን ነው፤ “ለእናንተ ዓለምን አሸንፌአለሁ፤ አይ ፣ ከአሁን በኋላ የራስችሁን ጦርነቶች መዋጋት የለባችሁም። እኔ እግዚአብሔር አምላክ - አዳኝሽና ጠባቂሽ ነኝ። እመኑኝ፣ ወደ እረፍቴም ግቡ። ቀላል ቀንበሬን ተሸክማችሁ፣ ጽድቅ ከእኔ ብቻ እንደ ሆነ አውቃችሁ፣ በእረፍት መውደድን ተማሩ” ይለናል።
እግዚአብሔር ጠባቂሽ መሆኑን አውቀሽ የዋህ እንድትሆኚ ዛሬ ደፋር እርምጃ እንድትወስጂ ላበረታታሽ እፈልጋለሁ። ይህ የዋህነት ከራሳችን፣ ከሌሎች እናም በተለይ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን መስተጋብር ሊተገበር ይገባል። አንቺን የሚጠብቅ አለ እና “በእግዚአብሔር የሚታመኑ አያፍሩም።”
ጸሎት
ጌታ ሆይ የማይንቀሳቀስ አለት፣ ታማኝ መካሪ ስለሆንክ አመሰግንሃለሁ። አንዳንድ ጊዜ በየዋህነት ኑሮን ማለፍ ቀላል አይደለም። ይህንን ግን ካንተ በላይ የሚረዳ ማንም የለም። ፍፁም እና ነቀፋ የሌለብህ ሆነህ ሳለህ፣ በትህትና፣ በየዋህነት እና ፍፁም በሆነ በአብ ተገዢነት በዚህ ምድር ተመላለስክ። ጌታ ሆይ ለአንተ እሰጥ ዘንድ ልቤን አስተምረው። ተመሳሳይ የዋህነት እንዲኖረኝ ልቤን አስተምረው። በመሸነፍ ማሸነፍ እንዳለ አስተምረኝ። በአንተ እንድረጋ ልቤን አበርታ። ጌታ ሆይ፣ እንዳንተ እንድሆን ልቤን አበረታ። አሜን