ስደት ምርጫቸው አልነበረም፤ የትውልድ ቀዬአቸውን ለቅቀው የሸሹት የሕጻኑን የኢየሱስ ክርስቶስን ነፍስ የሚፈልጋት ገዳይ ስለመጣባቸው ነበር (ማቴ 2፡13)፤ ምናልባትም ማርያም ጨቅላውን ተሸክማ ዳግም ስትንገላታ ልትወልድ ቀናት ሲቀሯት በአህያ ላይ ተቀምጣ አስቸጋሪ ጉዞ ያደረገችበትን ጊዜና ከቤተሰብ ርቃ በከብቶች በረት የተገላገለችበትን ጊዜ በአይነ ሕሊናዋ ሳትስል አትቀርም፡፡ ለአንዲት ወጣት እናት ከቤተሰብ ርቆ፣ ልጅ እንዴት እንደሚታቀፍ የምታሳይ እናት በሌለችበት መውለድ እንዴት ይከብዳል! (ሉቃ 2፡4-7) አራስ ልጅ ይዞ መሸሽስ እንዴት ፈተና ነው፣ ያውም ኖረውበት ወደማያውቁበት የሰው አገር! ቋንቋውና ባህሉ እንግዳ ወደሆነበት አገር! ይህ ሁሉ የጌታ ኢየሱስ ወላጆች ያለፉበት መከራ ነበር፡፡ የክርስቶስን ልደት በምናከብርበት በዚህን ጊዜ የማርያምና የዮሴፍ የመታዘዝ ሕይወትና አምላክ ለኛ ብሎ የከፈለው ዋጋ “አማኑኤል” የሚል መልዕክት አለው፡፡
ማርያም መልአኩ በተአምራዊ መንገድ እንደምትወልድ ሲነግራት ምንም እንኳ የታጨች ልጃገረድ ብትሆንም እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ብላ ተቀበለች፤ ዮሴፍ እጮኛው ማርያም ማርገዟንና እርሱም ወደቤቱ እንዲወስዳት ሲነገረው ታዘዘ፣ ሞኝነት ቢመስልም፣ አእምሮ ሊቀበለው የሚከብድ ቢሆንም ታዘዙ፤ ሕጻኑን ይዘው እንዲሸሹ ሲነገራቸውም አላመነቱም፤ ከስደት መልስ የትውልድ ሥፍራቸውን ትተው ናዝሬት እንዲኖሩ ሲነገራቸውም ታዘዙ፡፡
ማርያምና ዮሴፍ ሁሉ ግልጽ ሆኖላቸው ወይም ቀላል ሆኖ ስላገኙት አይደለም የታዘዙት፤ እንዲያውም ነገር እየከበደ የሄደ ነው የሚመስለው፤ ታዝዘው በስደት ወደ ግብጽ መውረዳቸው ከዚያም መልስ ከትውልድ ሥፍራቸው ርቀው በናዝሬት መኖራቸው ቀላል አይመስለኝም፡፡
በመከራ ማለፍ በእግዚአብሔር የመተው ወይም የመረሳት ምልክት አይደለም፤ እግዚአብሔርን መታዘዝ ለሥጋዊ መከራ ሊዳርግ ይችላል፤ ማርያምና ዮሴፍ የተሰጣቸው ጥሪ ኑሯቸውን አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡ አምላክ የሆነውን ክርስቶስን ተሸክመው ነው የተሰደዱት፡፡ እግዚአብሔር ወዴት ነው? ለሚለው ጥያቄአችን፣ ነገ ምን ይሆን? ለሚለው ስጋታችን ቃሉ አማኑኤል ይለናል! (ማቴ 1፡23) እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው፡፡ ስንጣል ከኛ ጋር ነው፤ ሰዎች ፊታቸው ሲቀየርብን ከኛ ጋር ነው፤ ስንፈራ፣ ኑሮ ፈተና ሲሆንብን ከኛ ጋር ነው፣ ግራ ስንጋባ ከኛ ጋር ነው፣ ስንደሰትም ከኛ ጋር ነው፡፡ አማኑኤል!
ጌታ ኢየሱስ ገና በጨቅላነቱ መሰደዱ ወላጆቹም ያዩት ፈተና ዛሬ ተመሳሳይ መከራ ውስጥ የሚገኙትን ወገኖች ያስታውሰናል፡፡ አገራችንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ብዙዎች ይፈናቀላሉ፣ ሳይወዱ ይሰደዳሉ፣ ይንከራተታሉ፡፡ ይህ የክርስቶስ ልደት መታሰቢያ ጊዜ እግዚአብሔር ከኛ ጋር (አማኑኤል) ያስታውሰናል! የምሥራቹ ተካፋዮች የሆንን እኛ የእግዚአብሔርን መገኘት የማብሰር ኃላፊነት አለብን፤ የተሰደዱትን በመርዳት፣ የተፈናቀሉትን በመደገፍ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝ አማኑኤልን እናብስር!
የአዳኙን የክርስቶስን ልደት በምናከብርበት በዚህ በተወደደ ጊዜ ጌታና ቤተሰቦቹ የከፈሉትን ዋጋ ማስታወስ ግራ በተጋባንበት ነገር ላይ የእግዚአብሔር መገኘት እንዳለ በመተማመን ወደርሱ እንድንቀርብ ያበረታታናል፤ ጠላት ሕጻኑን ኢየሱስን ሊያጠፋው አጥብቆ ቢጥርም የእግዚአብሔር ጥበቃ በርሱ ላይ ስለነበረ አመለጠ፡፡ ክፉ አጥብቆ መሞከሩ፣ ተስፋ ያለመቁረጡ፣ በተለያየ መንገድ ሰልፍ መክፈቱ ብቻ አያጠፋንም! አማኑኤል!
ከራሳችን አልፈን ደግሞ በጦርነትና በእርስበርስ ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የሰው እጅ የሚያዩትን፣ የሞቀ ቤታቸውን ጥለው ሸሽተው የዕለት ጉርስ ያጡትን፣ ቤተሰብ የሞተባቸውን፣ በታላቅ ስጋትና ጭንቀት ላይ ያሉትን ሁሉ ብናስብ መታዘዛችን ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር ይህን እንዳነደርግ እንዲረዳን፣ እንዲያበረታን፣ እና እንዲመራን ሁሌም እንጠይቀው፣ ፊቱንም እንፈልግ።
ጸሎት
እግዚአብሔር ሆይ፣ ፈቅደህ ዛሬን ስላየን፣ ስለያዝከን አመሰግንሀለሁ። ወደ ኢየሱስ ልደት እየተጠጋን ባለንበት በዚህ ጊዜ፣ ልባችንንና ቤታችንን ለተቸገሩት የምንከፍትበት፣ ያለንን የምናካፍልበት፣ የተጨነቁትን እህ ብለን የምናዳምጥበት፣ ስለሰላሙ አለቃ በቃልና በኑሮ የምንመሰክርበት በዓል ይሁንልን! አሜን።