Tuesday, 21 December 2021 03:00

ቀን 2:- ከያህዌ እስከ አማኑኤል

Written by

የስሜ ትርጉም ጥዑም ዜማ ነው:: ሆኖም አዚያሚ ወይም ዜማ አዋቂም አይደለሁም:: ስሜ እኔን ከሌሎች ሰዎች ከመለየት ውጪ ሌላ ምንም የሚናገረው ነገር የለም:: እንደውም በጣም  የተለመደ  ስም ስለሆነ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ ስም ያለን ሰዎች ስለምንኖር በስም ብቻ እኔን ለመለየት በቂ ስለማይሆን ሰዎች ሞክሼዎችን ለመለየት ተጨማሪ ግላጭ ቃላትን መጠቀም ግድ ይላቸዋል:: ስምና ህይወት ላይገናኝ ይችላል:: 

የእግዚአብሔር ስም ከስሞች ሁሉ የተለየ ነው:: የአሰያየሙ ሁኔታ ራሱ እጅግ ለየት ያለ ነው፤  እግዚአብሔር ራሱ ስምህ ማነው ተብሎ በቀጥታ በሙሴ ተጠይቆ ስሜ ያለና የሚኖር  ያህዌ ነኝ ብሏል:: ይህ ድንቅ ስም ከባድ የእግዚአብሔርን ባህሪ ተሸክሟል:: በማንም ያልተፈጠረ ጅማሬ የሌለው ስለዚህም ለዘላለም ለመቀጠል የማንምና የምንም እርዳታ የማያሻው ነገር ግን የሚታየውንም የማይታየውንም ህይወት ያለውንም ግዑዙንም የፈጠረ፣ ሲፈልግ በህይወት የሚያቆያቸው ሳያሻው መኖራቸውን ማቋረጥ የሚችል መጨረሻውም  የማይደረስበት ማለት ነው::

ይህ ማንነቱ የገነነው አምላክ ከእኛ ጋር ለመሆን የማይታመን ዋጋ ከፍሏል:: ሰውን መፍጠርና ሰውን መሆን የተለያዩ ናቸዉ:: እግዚአብሔር እኛን በፍጥረት ደረጃ ሳይሆን እንደኛው ሰው (ውስን) በመሆን ከእኛ ጋር ሆነ.፡፡ እንደሰው ልናልፍበት የምንችለውን መከራ ሁሉን በእያንዳንዱ መከራ ሰአት የሚሰማንን የስሜት መዋዠቅ ሁሉ እኛን ሆኖ እንዲያውቅ አርጎ ኖረ:: ለዚህም ነው የዕብራዊያን ፀሀፊ በነገር ሁሉ እንደእኛ ስለተፈተነ በድካማችችን ይራራልናል ያለን:: እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን ግን ወልድ ሰው መሆኑ ብቻ በቂ አልነበረም፤ ይልቁንም ሰው የመሆንን ፈተና ተቋቁሞ ፍፁም ቅዱስና ፃድቅ ሆኖ የደም ዋጋ ከፍሎ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነበር:: በዚህም ምክንያት ነው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ለመሆን የቻለው:: የዚህም አንዱ ትሩፋት ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎች ታላቁ እግዚአብሔርን አባት ወይም አባ ለማለት መቻላችን ነው:: 

ይህ ስሙ የገነነው እግዚአብሔር በዚህ ደረጃ ዋጋ ከፍሎ ከእኔ ጋር በግል ለመሆን ወስኗል፡፡ የኔ የሁልጊዜ ጥያቄዬ የእውነት እኔስ ከእርሱ ጋር ነኝ ወይ ነው፤ በዘላቂነት ወይም ባልተቆራረጠ ሁኔታ ከጌታዬ ጋር መሆን፣ ህልውና ውስጥ መዝለቅ የህይወቴ ተግዳሮት ነው:: ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆነው ደግሞ ዘላቂ የሆነ የፀሎትና የቃል ማንበብ ጊዜ የኖረን እንደሆን ብቻ ነው:: ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር መሆንን በሀሳብ ደረጃ እወደዋለሁ፣ እውነተኛ ፍላጎትም አለኝ ነገር ግን ፍላጎቴ ወደ ድርጊት እስካልተቀየረ ብዙ እውነተኛ ፍላጎት ስለመሆኑ እራሱ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል:: እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ለመሆን ዋጋ እንደከፈለው እኔም ከእርሱ ጋር ለምሆን የእውነት የምፈልግ ከሆነ የእርሱን ያህል እንኳን ባይሆን ዋጋ መክፈል ይኖርብኛል:: ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ከሌሎች ጋር ያለንን ጊዜ መቀነስ ግድ ይሆናል:: በጣም ባተሌ (busy) ሆነን ያለችን ጊዜ ለእንቅልፍ እንኳ የምንጠቀማት ከሆነም ከዚያች ጊዜ ቆርጠን ጊዜ መፍጠር ይኖርብናል::

እግዚአብሔር ከ2ሺህ ዓመት በፊት ከእኛ ጋር ለመሆን ወስኗል፣ የእውነት ብናስበው ደግሞ ከእኛ ጋር ለመሆን የወሰነው ገና ሳንፈጠር ነው፣ ገና በገነት ሳናጠፋ ነው፡፡ በዚህ የገና ወቅት ግን የፀሎት ህይወትሽ ምንም የደከመ ቢሆን፣ በብዙ ፈተና ክርስትናሽ የተፈተነም ቢሆን ወይንም በስንፍና ከባድ ብረት የታሰርሽ ቢመስልሽም የምህረት ደጅ ገና ስላልተዘጋ ጌታም ከአንቺ ጋር መሆኑን በአንቺ ምክኒያት ስላላቋረጠ ከእርሱ ጋር ለመሆን የምትወስኝበት ይሁን:: 

 

ጸሎት

እግዚአብሔር ሆይ፣ ተጠንቶ ታስቦ ስለማያልቀው ማንነህ አመሰግንሀለሁ። ስምህ ትልቅ ነው፤ ያኖርከኝም የያዝከኝም እንደ ምህረትህ ታላቅነት ነው፤ ተባረክ። እግዚአብሔር ሆይ፣ በልጅህ በኩል የከፈልክልኝን ዋጋ አስተውዬ፣ በልቤም ከብዶ፣ እኔም ለአንተ መስዋዕትነት የምከፍልበትን ልቦና ስጠኝ። ካሉብኝ የተለያዩ ጫናዎችና ፈተናዎች አምልጬ ከአንተ ጊዜ የማሳልፍበትን እድል እንዳገኝ እርዳኝ። ከአንተ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደገና ይጣፍጠኝ፣ ይናፍቀኝ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ እርዳኝ።   

 

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እኛም ከእርሱ ጋር! 

white-200.png

Serving Ethiopian women by encouraging and exemplifying vulnerable, thought-provoking conversations around the Gospel of Jesus Christ, the mission of the
Church, and the life of a Christian.

Address
:
Golagul Tower
Addis Ababa, Ethiopia

Emailinfo@selahethiopia.org
selahforethiopia@gmail.com

Follow Us

Subscribe to emails from Selah

We have officially launched our website and all our social media platforms. Please join us, follow, and share. Subscribe to our newsletter bringing you regular updates, resources, and everything in between!

Copyright © 2025 Selah Ministries.
Address: Addis Ababa, Ethiopia 
Emailinfo@selahethiopia.org