ትልቁ ሕልምሽ ምንድነው? ሕልምሽ ዕብደት መስሎ ተሰምቶሽ ያውቃል? ሁሌም ልታሳኪው እንደምትችዪ ይሰማሻል? በቀን ምን ያህል ጊዜ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብለሽ ትጠራጠሪያለሽ? ሸክሙ ከባድ ስለሆነ ስንት ጊዜ ትቼው በቃ “ተራ” ሰው ብሆንስ ብለሽ አስበሻል? እኔ ብዙ ጊዜ እንደዚህ አስቤያለሁ፡ ትልቅ ሸክም ስለሆነ በዚያ ፋንታ ተራ ሰው ብሆን ብያለሁ።
ሉቃስ 1፡28-35 ላይ በመልዓኩ ገብርዔልና በማርያም መካከል የተደረገ ደስ የሚል ንግግር እናገኛለን። ይህንን ክፍል በደንብ እናውቀዋለን፣ ግን ማርያም እንዴት እንደተቀበለችው ለማየት እስኪ ቀስ ብለን እናጢነው። ከማንኛውም ሰው እንደሚጠበቀው ማርያም ያልተጠበቀ ሰላምታውን ስትሰማ ደነገጠች (ቁጥር 29)፤ ከዚያም መልዓኩ አትፍሪ እንዳላት ስናይ እንደፈራች ማወቅ እንችላለን (ቁጥር 30)፤ በመጨረሻም አሁን ባለሁበት ሁኔታ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብላ ጠየቀች።
ይህ ከማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ምላሽ አይደል? ድንጋጤ፣ ፍርሃት፣ እንዴት እንዲህ ዓይነት ታላቅ ዕቅድ በእኔ ይሆናል ብሎ መጠየቅ።
መልዓኩ በቁጥር 35 ላይ ደስ የሚለኝን ምላሽ ሰጠ፡ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልልሻል” - ይህ ቀላል ንግግር አይደለም። ማርያም ምንም እንኳን እንደሌሎቻችን ሰው ብትሆንም የእግዚአብሔርን ልጅ ልትወልድ የቻለችው በዚህ ምክንያት እንደሆነ አምናለሁ።
“ይጸልልልሻል” የሚለውን ቃል ትርጉም ስንመለከት “መጠበቅ፣ መጋረድ፣ በጠባቂ ተጽዕኖ ሥር ማድረግ” የሚል ሃሳብ ነው። ይህ ማለት ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ሥር፣ በእርሱ ተጋርዳና ተከልላ እንደምትኖር ማረጋገጫ ተሰጥቷታል።
እኛም ይህ ማረጋገጫ አለን! ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክልን ነግሮናል (ዮሐንስ 14፡16፣ 26)፤ የመዳናችን ማረጋገጫ ማህተማችንም እርሱ ነው። (ኤፌ 1፡13-14)
ማርያምን ኃይል የሰጠው መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ከሆነ ለመውለድ የማይቻል ምን አለ? የትኛው ሕልም ለመሸከም አዳጋች ይሆናል? ምን ዓይነት ዓላማ የማይፈጸም ይሆናል?
ጸሎት
በታላቁ እግዚአብሔር ጥበቃና ክለላ ሥር ለመሆን ራሳችንን ሁልጊዜ እያቀረብን በውስጣችን ያስቀመጠውን ሕልም እንድንፈጽም እጸልያለሁ።
መልካም ገና!